1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የጋዛ ጦርነት እንዲቆም የሚጠይቁ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጥሪ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 28 2016

ጋዛም አስከሬን ተቀብሮባት፣ ቁስለኛ፣ ረሐብተኛ ተቆጥሮላት ሳያበቃ ተጨማሪ አስከሬን ይከመር-ፍርስራሽ ይቆለል፣ ቁስለኛ ይሰቃይባታል።ሬቤካ እንዳለችዉ ዛሬ ከሞተች እናት ማሕፀን ሳይወለድ እጓለ ሙት ህፃን ማዋለድ ለጋዛ ብርቅ አይደለም።8ኛ ወሩ።የጋዛን እልቂት የሚቃወመዉን ሕዝብ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከተቀየጡት ደግሞ ሁለት ሳምንት አለፋቸዉ።

https://p.dw.com/p/4fYjy
በተለያዩ ግዛቶችና ከተሞች የሚገኙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ፍልስጤሞች የሚደግፍ ሰልፍና አድማ አድርገዋል
የፍልስጤም ሕዝብን በመደገፍ የዩናይትድ ስቴትስ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ካደረጉት ሰልፍ አንዱ-ኒዉ ኦርሌንስምስል Chris Granger/AP Photo/picture alliance

ማሕደረ ዜና፣ የጋዛ ጦርነት እንዲቆም የሚጠይቁ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጥሪ

ብዙዎች የጋዛ ጦርነት፣ ሌሎች የእስራኤል-ሐማስ ዉጊያ፣ ሌሎች የጋዛ «ዘር ማጥፋት» የሚሉትን ጥፋት በመቃወም ካለፈዉ መስከረም ማብቂያ ወዲሕ ሰልፍ ያልተደረገባቸዉ ትላልቅ ከተማ-አደባባዮች የሉም።ሰሞኑን ደግሞ ተረኛ ተቃዋሚዎቹ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸዉ።ባለፈዉ ሳምንት ከሐቫና እስከ ባግዳድ፣ ከፓሪስ እስከ ኒዩዮርክ የሚገኙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በጋዛ ሕዝብን ላይ የሚደርሰዉን እልቂት፣ ሥቃይ ሰቆቃና ግፍ አዉግዘዋል።ለፍልስጤሞች ያላቸዉን ድጋፍ ገልጠዋል።የተማሪዎቹን ጥያቄ፣ አድማና መልዕክትን የተቃወሙም አልጠፉም።ከፍተኛ ተቃዉሞ የተቀሰቀሰባት የዩናይትድ ስቴትስ ፀጥታ አስከባሪዎችም ከ2400 በላይ ተማሪዎች አስረዋል።አንዳድ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢና አጠገብ የተተከሉ ድንኳንና ዳሶችን አፍርሰዋልም።የተማሪዎቹ ተቃዉሞ፣ የተቃዉሞዉ ተቃዉሞና የመናገር ነፃነት አተረጋጎም ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።
 

ሬቤካ ባሚዴል እናትም-ተማሪም፣ ጥቁርም-አሜሪካዊም ናት።ቦስተን-ማሳቹስተስ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘዉ የኖርዝ ኢስተርን ዩኒቨርስቲ ባለፈዉ ቅዳሜ ያስመራቃቸዉን ተማሪዎች ወክላ ባደረገችዉ ንግግር ሁሉንም አለችዉ።

«አሁን እኔ እዚሕ ቆሜ ለናንተ ስናገር ሕፃናት ፍርስራሽ መሐል  በባትሪ ርዳታ ይወለዳሉ።ከተወለዱ በኋላ እንኳ ረሐብና ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያጋጥማቸዋል።እናቶች ህክምና ስለማያገኙ በወሊድ መዛባት ደም እየፈሰሳቸዉ ይሞታሉ።እንደ ጥቁር እናቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በ2020 እንደተገነዘብኩት የእነዚሕ እናቶችና ሕፃናት ሕይወት ለአደጋ የተጋለጠዉ በነሱ ጥፋት አይደለም።በተቋማት፣ በአድሏዊነትና በፍትሐዊነት እጦት እንጂ።እና ጋዛ ዉስጥ ዘላቂ ተኩስ አቁም እስካልተደረገ ድረስ ጋዛ የሚኖሩ እናቶችና የመላዉ የጋዛ ሕዝብ በየዕለቱ ለአደጋ እንደተጋለጠ ነዉ።»


የሐማስ ጥቃትና መዘዝ 

እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ተከታዮቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ ባለፈዉ መስከረም 26 ደቡባዊ እስራኤልን ወርሮ 1 ሺሕ 200 ያክል ሰዎችን መግደል፣ በመቶ የሚቆጠሩ ማገቱን ያላወገዘ፣ ለእስራኤል ድጋፉን ያልሰጠ መንግስት ሲበዛ ጥቂት ነዉ።
ከጅምሩ የሐማስና የኢስላሚክ ጀሐድን ጥቃት ለመበቀል ያለመ መስሎ የነበረዉ የእስራኤል መንግሥት አፀፋ ጥቃት በጊዜ ሒደት ወትሮም በእስራኤል ከበባና እመቃ ምክንያት «የዓለም ትልቁ ጣራ የለሽ እስር ቤት» የምትባለዉን ጋዛን አዉድሟታል።የእስራኤል ጦር ጥቃት የዚያች ጠባብ፣ ትንሽ፣ ቀጭን ሰርጥ መከረኛ ሕዝብን ዕለት በዕለት እያረገፈ፣ እያፈናቀለ፣ በረሐብ እየጠበሰዉ ነዉ። 

ፖሊስ በርካታ ጊዚያዊ ሰፈሮችን አፍርሷል፤ ከ2400 በላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን አስሯልም
የዩናይትድ ስቴትስ ፖሊስ ፣ ተማሪዎች የመሰረቷቸዉን የመቃወሚያ ሰፈሮች ሲያፈርሱምስል Etienne Laurent/AFP

ለእስራኤል ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ ጠንካራ ድጋፍ የሚሰጠዉ የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ዮሴፍ ቦርሪል ባለፈዉ መጋቢት እንዳሉት ጋዛ ለነዋሪዎችዋ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሕጎችና መርሆችም «የዓለም ትልቅ ጣራ የለሽ መቀበሪያ ሆናለች።»

«ጋዛ ከጦርነቱ በፊት ትልቁ ክፍት እስር ቤት ነበረች።ዛሬ ትልቁ ክፍት የመቃብር ሥፍራ ናት።በብዙ አስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች፣ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎቹ በጣም አስፈላጊ ለሆኑ የሰብአዊነት ሕጎች መርሕም ጭምር የመቃብር ሥፍራ ሆናለች።»

የዓለም ፖለቲከኞች ጥሪ፣ የሕግ አዋቂዎች አቤቱታ፣ የዓለም ማሕበራት ምክር፣ የመብት ተሟጋቾች ማሳሰቢያ፣ የዓለም ሕዝብ  የአደባባይ ተቃዉሞ፣ የዓለም ፍርድ ቤት ዉሳኔ፣ ማሳሰቢያምና ማስጠንቀቂያ በየመገናኛ ዘዴዉ እየጎረፈ ከአድማጭ-ተመልካቹ ጆሮ ጋር እየተላተመ ይበናል።

 ተቃዉሞዉ በሌሎች ሐገራትም ተዛምቷል

ጋዛም አስከሬን ተቀብሮባት፣ ቁስለኛ፣ ረሐብተኛ ተቆጥሮላት ሳያበቃ ተጨማሪ አስከሬን ይከመር-ፍርስራሽ ይቆለል፣ ቁስለኛ ይሰቃይባታል።ሬቤካ እንዳለችዉ ዛሬ ከሞተች እናት ማሕፀን ሳይወለድ እጓለ ሙት ህፃን ማዋለድ ለጋዛ ብርቅ አይደለም።8ኛ ወሩ።የጋዛን እልቂት የሚቃወመዉን ሕዝብ  የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከተቀየጡት ደግሞ ሁለት ሳምንት አለፋቸዉ።

የዩናይትድ ስቴትስ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የጀመሩት ተቃዉሞ በበርካታ ሐገራትና ከተሞች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በየመማሪያ ክፍሎች፣ በየድንኳን ሠፈሩ፣ በየመመሪቂያዉ ድግስና አዳራሽ፣ አደባባይም  ቀጠሏል።ሐቫና ኩባ-ባለፈዉ ሳምንት አርብ።
                                   
የተማሪዎች  ፌደሬሽን ፕሬዝደንት ሆዜ አልቤርቶ አል ሜይዳ እንደሚለዉ የጋዛ ህዝብ ዕልቂትን እየሰሙ ዝም ማለት ይቅርታ ሊደረግለት አይገባም።«ጧት  በነቃን ቁጥር ዛሬ ጋዛ ዉስጥ ሥለሚፈፀመዉ ዘር ማጥፋት፣ ልጆች፣ወጣቶች፣አዛዉንቶች፣ መገደላቸዉ መቀጠሉን እያወቅትን ለተጠማሪ ቀን ከዕንቅልፋችን መንቃቱ ይቅርታ ሊደረግለት አይገባም ብለን እናስባለን።እኔ ዛሬ እዚሕ ዩኒቨርስቲ መሆኔን አዉቃለሁ፣ ነገም እዚሁ እንደምሆን አዉቃለሁ።ጋዛ ያሉ ባልጀሮቼ ምን እንደሚገጥማቸዉ፣ በፍልስጤሞች ላይ የሚደርሰዉን የዘር ማጥፋት፣ ጭቆና በደልን የሚቃወሙት ዩናይትድ ስቴትስ ባልጀሮቼ ምን እንደሚያደርጉ ግን አላዉቅም።»

የዩናይትድ ስቴትስ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባደረጉት ጥሪ መሠረት የበርካታ ሐገራት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የእስራኤልና የደጋፊዎችዋን እርምጃ ተቃዉመዋል።
በፍልስጤም ሕዝብ ላይ የሚደርሰዉ ግፍ በመቃወም የሜክሲኮ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ካደረጉት ተቃዉሞ አንዱምስል Yuri Cortez/AFP/Getty Images

ቅዳሜ። ባግዳድ-ኢራቅ።ከመካከለኛዉ ምስራቅ አንጋፋና ዕዉቅ ዩኒቨርስቲዎች አንዱ የሆነዉ የባግዳድ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ተቃዉሞዉን የጀመሩትን የዩናይትድ ስቴትስ ተማሪዎችን ያመሰግናሉየዩናይትድ ስቴትስን መንግስት ግን ያወግዛሉ።ከተቃዉሞ ሰልፈኞቹ አንዷ አያ ቀድር እንደምትለዉ የፍልስጤሞች ጉዳይ የአረብ ወይም የሙስሊሞች ጉዳይ ብቻ አይደለም።
«የፍልስጤሞች ጉዳይ የአረብ ወይም የሙስሊሞች ጉዳይ ብቻ አይደለም።የሰብአዊነት ጉዳይ እንጂ።ሥለዚሕ በፍልስጤም ሕዝብ ላይ የሚደርሰዉ ግፍ እስኪቆም ድረስ ለፍልስጤሞች የምንሰጠዉ ድጋፍ ይቀጥላል።»

የአረቦች አቋም፣ የተማሪዎቹ  ፅናት

ኢራቅ ፈርሳለች።ሶሪያ ወድማለች።የመን ጠንካራ መንግስት የላትም።የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከሶማሊያ-እስከ የመን፣ ከሱዳን እስከ ኢትዮጵያ እስከ ሊቢያ ያሉ ግጭት፣ ዉጊያ፣ ጦርነቶችን ታቀጣጥላለች።ቀጠር እስራኤል ሐማስን ለማስታረቅ ስትዳርክ የዓለም አቀፍ ቴሌቪዥን ጣቢያዋ ጋዜጠኞች ጋዛ ላይ ይገደላሉ።አሁን ደግሞ የአልጀዚራ ቴሌቬዥን ጣቢያ ሥርጭት እስራኤል ዉስጥ ትናንት ተዘግቷል።
የባሕሬን፣ የኦማን፣የኩዌት፣ የሳዑዲ አረቢያ ነገስታት ሕዝባቸዉን አፍነዉ፣ እነሱም ታፍነዉ ዕለታት ይቆጥራሉ።ማሕሙድ አባስ ረመላሕ ዉስጥ ተኮድኩደዉ  የሚቆረጥላቸዉን ዶላር ይቆጥራሉ።ንጉስ አብደላሕ ወደ እስራኤል የሚተኮስ ሚሳዬል ያስከሽፋሉ።የቀድሞዉ ፊልድ ማርሻል አል ሲሲ የግብፅ ሕዝብን ልሳንም፣ የሲና ጠረፍንም ዘግተዉ እርጥባን ይቀበላሉ። 
ፍልስጤምን ከሩቅ የሚያዉቁት የአዉሮጳ አሜሪካ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ይጮኻሉ።ደብሊን-አየር ላንድ-ትሪኒቲ ኮሌጅ-ቅዳሜ።
የማንቼስተር-ብሪታንያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከአደባባይ ሰልፍ በተጨማሪ ልክ እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ብዜዎቻቸዉ ሁሉ ሠፈር (ካምፕ) መስርተዉ የጋዛን እየተቃወሙ ነዉ።የፓሪስ-ፈረንሳይም ተማሪዎችም እንዲሁ።በሌሎችም ሐገራት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቃዉሞ ቀጥሏል።

የተቃዉሞዉ ጀማሪዎች፣ የሌሎቹ ሐገራትን ተማሪዎች ትብብር ጠያቂዎችም ግን የዩናይትድ ስቴትስ ዩኒቨርስቲና ኮሌጆች ተማሪዎች ናቸዉ።ሚያዚያ አጋማሽ ላይ የተጀመረዉ ተቃዉሞ እስከ ትናት ዕሁድ ድረስ የ60 ዩነቨርስቲ፣ የኮሌጅጄችና የግቢ ወይም ካምፓሶችን ተማሪዎች አዳርሷል።ተማሪዎቹ ፍልስጤሞችን በመደገፍ በተለይ በጋዛ ሕዝብ ላይ  የሚደርስባቸዉን በመቃወም እየጮኹ ነዉ።

የፈረንሳይ ፖሊስ የተማሪዎቹን ተቃዉሞ እንቅስቃሴ ገድቦታል።
የፓሪስ-ፈረንሳይ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ፍልስጤሞችን በመደገፍ ካደረጉት ስብሰባ አንዱምስል Luc Auffret/Anadolu/picture alliance

የተቃዉሞዉ ተቋዉሞ፣ የባይደን ማሳሰቢያ

ኢሊኖይስ-ችካጎን በመሳሰሉ አካባቢዎች የእስራኤልን እርምጃ የሚደግፉ ወገኖች የተማሪዎቹን ጥያቄና ተቃዉሞ በመቃወም ተሰልፈዋል። ተማሪዎቹን በፀረ-ሴማዊነት፣ በሐማስ ደጋፊነት፣በትምሕርትና ምረቃ አደናቃፊነት የሚተቹና የሚወቅሷቸዉም አሉ።ፖሊስም ከ2400 በላይ ተማሪዎችን ማሰሩ ተዘግቧል።ተማሪዎቹ በተለያዩ ዩኒቨርስቲና ኮሌጆች ቅጥር ግቢ ወይም አካባቢ የመሰረቷቸዉን ጊዚያዊ ሠፈሮች አፍርሷልም።

የአሜሪካ ዜና አገልግሎት አሶስየትድ ፕሬስ እንደዘገበዉ የተቃዉሞ ጥሪ፣ሰልፍ፣ አድማ፣ እንቅስቃሴን ማወክ፣ ወይም ባንፃሩ ተቃዋሚዎችን መቃወም፣ ማዉገዝ፣ የፀጥታ አስከባሪዎች እርምጃም ለአሜሪካ የዛሬ መልክና ባሕሪዋን የሰጣት የታታላቅ ታሪኳ አካል ነዉ።ፕሬዝደንት ጆ ባይደንም ይሕን አረጋገጠዋል።
ይሁንና ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ለቤንያሚን ኔታንያሁ መንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ በመሰጠታቸዉ የመብት ተሟጋቾች የሚወቅሷቸዉ ባይደን አገም-ጠቀም በመሰለ ንግግራቸዉ ተማሪዎቹን ተችተዋል።

«የመቃወም መብት አለ።ሁከት የመፍጠር መብት ግን የለም።ሰዎች የመማር፣ዲግሪ የማግኘት፣ በየዩኒቨርስቲዎቹ ቅጥር ግቢ በሰላምና ጥቃት ይደርስባናል ከሚል ፍራቻ ነፃ ሆነዉ የመጓዝ መብት አላቸዉ።ሥለዚሕም ጉዳይ ግልፅ ልንሆን ይገባል።በየትኛዉም ግቢ፣ በመላዉ አሜሪካም ለፀረ-ሴማዊነት ወይም በአይሁድ ተማሪዎች ላይ ለሚፈፀም አመፃ ቦታ የለም።ለጥላቻ ንግግር ወይም ፀረ ሴማዊነት ይሁን፣ እስላም ጥላቻ ወይም በአረብ ወይም በፍልስጤም አሜሪካዉያን ላይ ለሚደርስ በደል ወይም ለየትኛዉም ዓይነት ሁከት ቦታ የለም።»

ፍልስጤሞች በመደገፍ የተለያዩ ሐገራት ተማሪዎች ከመሰረቱት ጊዚያ መንደር አንዱ-ኒዉካስል-ብሪታንያ
የኒዉካስል-የብሪታንያ ተማሪዎች በፍልስጤሞች ላይ የሚደርሰዉ ግፍ በመቃወም ከመሠረቱት የድንኳን ሠፈር አንዱምስል Owen Humphreys/PA Wire/empics/picture alliance

የዩናይትድ ስቴትስ ህዝብ በመጪዉ ሕዳር የወደፊት መሪዉን ይመርጣል።ባይደን የያዙትን የፕሬዝደንትነት ሥልጣን እንደያዙ ለመቀጠል፣ ምናልባት ዶናልድ ትራምፕ ከሶስት ዓመት በፊት ያጡትን ሥልጣን ለመያዝ እየተፋለሙ  ነዉ።ከዩክሬን እስከ ጋዛ በሚደረገዉ ጦርነት የተዘፈቁት ታዛቢዎች እንደሚሉት ባይደን አንዱም ጋ ለድል ሳይበቁ፣ ካንዱም ሳይሆኑ እንዳይቀሩ የተማሪዎቹን ተቃዉሞ ለእስራኤል ከሚሰጡት ዙሪያ መለስ ድጋፍ ጋር ለማጣጣም እየጣሩ ነዉ።ጋዛ ግን በተለይ ራፋሕ ላይ ለተጨማሪ እልቂት እየተሞሸረች ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ 

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር