1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብርቱ ዝናም ተፈናቃዮችን ከድንኳናቸውም አፈናቀለ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 24 2016

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ ትናንት ነፋስና በረዶ የቀላቀለ ዝናብ የተፈናቃዮችን ድንኳን አፈራረሰ ።ብርቱው ዝናም ሐይቅ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘውና በተለምዶ «ቱርክ» እየተባለ በሚጠራው የተፈናቃዮች መጠለያ ላይ ጉዳት ማድረሱን ተፈናቃዮች ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4fQns
የሰሞኑ ብርቱ ዝናም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ኃይለኛ የጎርፍ መጥለቅለቅና ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ። ፎቶ፦ ከማኅደር
የሰሞኑ ብርቱ ዝናም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ኃይለኛ የጎርፍ መጥለቅለቅና ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል privat

ብርቱው ዝናም በየቦታው የጎርፍ መጥለቅለቅና ጉዳት አድርs4ል

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ ትናንት ነፋስና በረዶ የቀላቀለ ዝናብ የተፈናቃዮችን ድንኳን አፈራረሰ ። ብርቱው ዝናም ሐይቅ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘውና በተለምዶ «ቱርክ» እየተባለ በሚጠራው የተፈናቃዮች መጠለያ ላይ ጉዳት ማድረሱን ተፈናቃዮች ተናግረዋል ። የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ጉዳቱን የሚያጠና ቡድን ወደ ቦታው መላኩን አስታውቋል ። 

ተፈናቃዮች በድንኳን ቢጠለሉም ድንኳናቸው ፈራርሷል

ተፈናቃዮቹ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ትናንት ከሰዓት በኋላ በተፈናቃዮች መኖሪያ አካባቢ ከፍተኛ ወጀብና በረዶ የቀላቀለ ዝናብ በመጠለያ ጣቢያው ባሉ በርካታ የተፈናቃዮች መኖሪያ ድንኳኖች ላይ ጉዳትአድርሷል፣ ለምግብነት የተቀመጡ የምግብ ዓይነቶችም በጎርፍ ተወስደዋል፣ ህፃናት ወላዶችና ነፍሰ ጡር ተፈናቃዮች ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል፡፡

"... መጀመሪያ እንደነፋስ አድርጎ ጀመረ፣ በመጨረሻ ድንኳኑን አንድ በአንድ ጉዳት አደረሰበት፣ በተለይ በረዶው ነው የጎዳን፣ ለምግብነት የተሰጠን ነገርም በጎርፍ ተወሰደ፣ ድንኳን በአጠቃላይ ወድሟል በተለይ ህፃናት፣ "ሩሀቸው” (ነፍሳቸው) ብቻ ነው ያለው፣ አሁን መጠለያ አጥተን ነው ያለነው፡፡” ብለዋል፡፡

በመጠለያ ጣቢያው ከነበሩትና መኖሪያ ድንኳናቸው በከባድ ዝናብ ከፈረሰባቸው ተፈናቃዮች መካከል ለዶቼ ቬሌ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ ተፈናቃይ እንዳሉት "በጣለው ከባድ ዝናብ የሰው ህይወት ባይጠፋም 2ሺህ ያህል ሰዎች ድንኳናቸው የፈረሰ ሲሆን ካሉት 450 ያክል መጠለያ ድንኳኖች መካከል 160 የሚሆኑት ፈራርሰዋል፡፡”

የአማራ ተፈናቃዮች በተለያዩ መጠለያዎች ይገኛሉ ። ፎቶ፦ ከማኅደር
የአማራ ተፈናቃዮች በተለያዩ መጠለያዎች ይገኛሉ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Alamata City Youth League

ብርቱው ዝናም 160 ድንኳኖችን ከጥቅም ውጪ አድርጓል

" ትናንት ከ10 እስከ 12 ፡30 ሰዓት ከሰዓት በኋላ በረዶና ነፋስ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ "ቱርክ” የተፈናቃዮች መጠለያ ላይ ጉዳት አድርሷል፣ ወደ 165 ድንኳኖች ውስጥ የነበርን 2ሺህ 600 ያህል ተፈናቃዮች ያለመጠለያ ቀርተናል፤ ነፋሱ ድንኳኑን እየገነጣጠለ ነው የወደሰደው፣ የነበረ ዱቄትና ጥራጥሬም በጎርፍ ተወስዶ ደለል ሆኗል” ነው ያሉን፡፡

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ተፈናቃይ በበኩላቸው፣ በደረሰው አደጋ ብዙ ሰዎች ያለመጠለያ መቅረታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዋ፣ ነፋሱም ሆነ በረዶው ትልቁንም ትንሹንም ድንኳን ገነጣጥሎ ጥሎታል፣ ሽማግሌውም፣ ሶብዩም (ህፃናቱ) የሚጠለልበት አጥቶ በብረድድ ይንሰፈሰፋል ሲሉ ነው የገለጡት፡፡

በአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የደቡብ ወሎ ዞን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ሙሐመድ ሰኢድ አደጋው መድረሱን ሪፖርት እንደደረሳቸው ጠቁመው፣ አጠቃላይ ደረሰውን ጉዳት መጠን የሚያጠና ቡድን ወደ ቦታው ተልኳል ብለዋል፡፡

በተወጠሩ ድንኳኖች ውስጥ የአማራ ተፈናቃዮች
በተወጠሩ ድንኳኖች ውስጥ የአማራ ተፈናቃዮች በተለያዩ መጠለያዎች ይገኛሉ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Alamata City Youth League

በአብዛኘው የፈረሱት ከ2 ዓመታት በፊት የርዳታ ድርጅቶች የሠሯቸው ናቸው

" ኃይለኛ ወጀብ ስለነበር፣ ድንኳኖቹን ነቃቅሎ አስቀምጧቸዋል፣ የተረፉ ትናንሽ ድንኳኖች አሉ፣ ትላልቅም አሉ፣ በአብዛኘው የፈረሱት ከ2 ዓመታት በፊት የርዳታ ድርጅቶች የሠሯቸው ናቸው፣ አጠቃላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ቡድን ከተለያዩ ተቋማት ተውጣጥቶ ተልኳል ምላሽ እየጠበቅን ነው፣ ሰዎቹ ለጊዜው በቢሮዎች፣ በመጋዝኖች እንዲጠለሉ ተደርጓል፣ የጥናት ቡድኑ ሲመለስ የጉዳት መጠኑ ታይቶ ዘላቂ ወይም ጊዜያዊ መፍትሔ ይፈለጋል፡፡” ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልልና ከአማራ ክልል ውጪ በነበሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ 622 ሺህ ወገኖች በክልሉ  የተለያዩ አካባቢዎች በመጠለያና ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንደሚሩ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ሰሞኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ